በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ በጀት የመስኖ ፕሮጀክቶች እንደሚከናወኑ ተገለጸ

ባህር ዳር ፤ መስከረም 24/2017- በአማራ ክልል በተያዘው የበጀት ዓመት ከአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በሚበልጥ በጀት የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ፣ ጥገናና የዲዛይን ስራዎች እንደሚከናውኑ የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ ለአርሶ አደሩ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ክረምት ከበጋ አምርቶ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ እየተሰራ መሆኑን የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አየልኝ መሳፍንት ለኢዜአ ተናግረዋል።

ለዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ 154 ነባርና አዳዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የመስኖ ፕሮጀክቶችም ከ23 ሺህ 600 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት እንደሚያስችሉ ጠቅሰው፤ ከ49 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን የዘመናዊ መስኖ ልማት ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በዚህም ተሳታፊ አርሶ አደሮች በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ በማምረት ከራሳቸው በመትረፍ ለገበያ እንዲያቀርቡ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ከሚገነቡት ፕሮጀክቶች መካከልም አራት ሺህ 620 ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችሉ 98 የመስኖ ፕሮጀክቶች በበጀት ዓመቱ ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በ377 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በጀት የ108 የመስኖ ፕሮጀክቶች ጥገናና ዲዛይን ስራ እንደሚከናወን አቶ አየልኝ መሳፍንት ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥም 82 የሚሆኑት ለቀጣይ ዓመታት ግንባታ የሚውል፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ነባርና የተባለሹ ፕሮጀክቶች ጥገና እንደሆኑ ተናግረዋል።

በየዓመቱ እስከ ህዳር 30 ያለው ጊዜ የቅድመ ዝግጅት ወቅት ነው ያሉት አቶ አየልኝ፤ እስካሁንም የእቅድ ትውውቅ፣ የዲዛይን ማሻሻልና በዚህ ዓመት የሚጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን የመለየት ስራ መከናወኑን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም አዳዲስ ለሚገነቡ ፕሮጀክቶች ጨረታ በማውጣት አሸናፊውን የመለየት ስራ ከመከናወኑም በላይ የዲዛይንና የክትትል ባለሙያዎች በ”ሶፍት ዌር” የታገዘ ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን አመልክተዋል።

ይህም የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ጥራትን በማስጠበቅ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁና የሚስተዋሉ ችግሮችን ፈጥኖ በመፍታት አቅም ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ከክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በሚበልጥ በጀት የተለያዩ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ማከናወን ተችሏል።

ኢዜአ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top