ባሕር ዳር: መስከረም 25/2017 ዓ.ም
የአማራ ክልል መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ የ2016 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 ዓ.ም ዕቅድ ትውውቅ የሦስትዮሽ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።
በክልሉ በሚካሄዱ የተቀናጁ የመሰኖ ልማት ሥራዎች በግንባታ ሂደት፣ በግንባታ ባለቤት፣ ተቋራጭ እና አማካሪ መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን አውቆ ውሳኔ ለመስጠት ያስችል ዘንድ ነው ከአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደ ያለው።
በምክክሩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢንጅነር ዳኝነት ፈንታ (ዶ.ር) የመስኖ ሥራ የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ድጋፍ እና ትብብር እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
ክልሉ ከ2018 ዓ.ም ጀምሮ የሚተገበር የአምስት ዓመታት የስትራቴጅክ ዕቅድ ማዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።
የስትራቴጅክ ዕቅዱን በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር 2017 ዓ.ም የዝግጅት ምዕራፍ እንደሚኾን ነው የተናገሩት።
በዓመቱ የታቀዱ ዕቅዶችን በላቀ ደረጃ ለመፈጸም ቅድመ ዝግጅት አስፈላጊ መኾኑንም ነው የገለጹት።
በተግባር ምዕራፍ የተሟላ ሥራ ለመሥራት በዕቅዶች ላይ መግባባት እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል።
በ2016 ዓ.ም የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን የበለጠ ማዳበር፤ የነበሩ ድክመቶችን ደግሞ መፍታት ይገባል ነው ያሉት።
የመስኖ ፕሮጀክቶች አስቸጋሪ የቦታ አቀማመጥ ያለባቸው እና ለእንቅስቃሴ ምቹ ባልኾኑ አካባቢዎች የሚፈጸሙ በመኾናቸው የባለድርሻ አካላትን ትብብር በከፍተኛ ሁኔታ ይጠይቃሉ ነው ያሉት።
በተለይም የተጠቃሚውን ሕዝብ ትብብር እንደሚፈልጉም አብራርተዋል።
የመስኖ ተጠቃሚው ሕዝብ ባለቤት ኾኖ የመስኖ ፕሮጄክቶችን እንዲሠራም አስገንዝበዋል።
የምክር ቤት አባላት ደግሞ ሕዝብ የፕሮጄክቶቹ ባለቤት እንዲኾን እንዲሠሩም ጠይቀዋል።
ቢሮው ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ሥራዎችን እንደሠራ የተናገሩት ኀላፊው የክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት ከሚፈልገው አንጻር ግን በርካታ ያልተሠሩ ሥራዎች አሉ ነው ያሉት።
ያደሩ ሥራዎችን መፈጸም እና አዳዲስ ሥራዎችን ደግሞ በተገቢው መልኩ መከወን ያስፈልጋል ብለዋል።
መስኖ ለሀገር ዕድገት ቁልፍ ሚና ይጫወታልም ነው ያሉት።
መስኖ ምጣኔ ሃብታዊ ብቻ ሳይኾን ማኅበራዊ ጠቀሜታውም የጎላ መኾኑን ተናግረዋል።
አንድ ማኅበረሰብ በምጣኔ ሃብት ሲያድግ ማኅበራዊ ትስስሩም የጠነከረ ይኾናል ነው ያሉት።
ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለውን መስኖ ማገዝ፣ መደገፍ የተሻለ ደረጃ እንዲደርስም ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
አሚኮ