በደሴ ዙሪያ ወረዳ በ62 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የመስኖ ፕሮጀክት ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።
ጥር 13/2017 ዓ.ም በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ዙሪያ ወረዳ በ62 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የመስኖ ፕሮጀክት ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል።
የበደሴ ዙሪያ ወረዳ የሰፋያት ቀበሌ ነዋሪዎች የተገነባው የመስኖ ፕሮጀክት ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ በዓመት ሁለት ጊዜ እና ከዚያ በላይ ለማምረት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አሊ ይማም በዞኑ 16 የመስኖ ፕሮጀክቶች በመገንባት ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል። ዛሬ የተመረቀው የየጀርቲ መስኖ ፕሮጀክት 192 ሄክታር መሬትን የሚያለማ መኾኑን ገልጸዋል።
በአካባቢው የሚገኙ አርሶአደሮችን በማኅበር በማደራጀት ወደ ሥራ እንደሚገባ የተናገሩት ምክትል አሥተዳዳሪው የዞኑን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግም ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢንጂነር ዳኝነት ፈንታ (ዶ.ር) ፕሮጀክቱ ከ62 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ገልጸዋል። ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ የድጋፍ እና ክትትል ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ለረጅም ዓመታት አገልግሎት እንዲሰጥ እንክብካቤ እና ጥበቃ እንዲደረግለት በዙሪያው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች ሊሠሩ እንደሚገባም ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ ልማቱን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ለሰላም መጠበቅ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም አሳስበዋል።
ዘገባው የአሚኮ ነው