በትላልቅ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ዙሪያ በአፈፃፀም ችግሮቻቸው እና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የከፍተኛ አመራሮች ምክክር መድረክ ተካሄደ።
ታህሳስ 12/2017 ዓ.ም ባህርዳር። በአማራ ክልል በመገንባት ላይ ያሉና በበጀት ዓመቱ የሚገነቡ አዲስ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ ርዕሠ መስተዳድር አረጋ ከበደ በሚመሩት እና የቢሮ ኋላፊዎች የዞን ዋና አስተዳዳሪና ከንቲባዎች የተካፈሉበት የፕሮጀክቶች አፈፃፀም ግምገማ ሪፖርት ቀርቦ በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ የምክክር መድረክ ተካሄዷል።
በመድረኩ ሪፖርት ካቀረቡ ጥቂት ተቋማት መካከል የመስኖና ቆላማ አካ/ል/ቢሮ አንዱ ሲሆን የቢሮ ኋላፊው ዶ/ር ኢንጅነር ዳኝነት ፈንታ በአጠቃላይ የክልላችን የመስኖ ውሃ ፀጋዎች ዙሪያ እና እስካሁን ባሉ አፈፃፀሞች እንዲሁም የእያንዳንዱን ዞን ነባር እና አዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶች ዕቅድ እንዲሁም በፌደራል የተያዙ ሜጋ የመስኖ ጥናትና ዲዛይንና የግንባታ ሥራዎች ዙሪያ አጭር ሪፖርት ቀርቦ አቅጣጫ ተመላክቷል።
ዶ/ር-ኢ ዳኝነት እንደገለፁት ክልላችን ምንም እንኳን ሠፊ የውሃ ሃብት እና በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት ቢኖርም እስካሁን በመስኖ የለማው መሬት ከ110 ሺህ ሄ/ር በላይ እንደማይበልጥ እና ሠፊ ያልተጠቀምንበት የውሃ ሃብት እንዳለን በመጠቆም መስኖ ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ በመጠጨመር ፤ የኑሮ ውድነትን በማሻሻል ፤ እንዲሁም የወጣቶች የሥራ ዕድል በስፋት በመፍጠር በኩል ሚናው የጎላ መሆኑን የገለፁ ሲሆን ሠላምን በዘላቂነት በማረጋገጥ በኩልም ድርሻው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዶክተር ዳኝነት አያይዘውም ለነባር መስኖ ፕሮጀክቶች እና አዲስ ፕሮጀክቶች ከጥናት እስከ ግንባታ ሥራ ለቢሮው ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ መመደቡን በመጠቆም በፌደራል መስኖና ቆላማ አካባቢ ሚንስቴር በሚገነቡ ሜጋ መስኖ ፕሮጀክቶች በድምሩ ከ11.8 ቢሊየን ብር በላይ ለዚህ ዓመት ብቻ በጀት መያዙን በመግለፅ በክልላችን የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በፕሮጀክቶቹ የነዳጅ አቅርቦት ላይ፤ በማሽነሪ ዝውውር ችግር ፈጥሮ እንደነበር ጠቁመው በሌላ በኩል መሬት ከሦስተኛ ወገን ነፃ ያለማድረግም በአፈፃፀሞቹ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደነበረው በመግለፅ የፕሮጀክቶቹ መቋረጥ ወደ ለክልላችን የሚመጣን ሃብት በመጠቀምና ድህነትን በዘላቂነት ለመቅረፍ በሚደረግ ትግል ውስጥ አሉታዊ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ጠቁመው የዞን አስተዳዳሪዎች እስከታች ድረስ ለመስኖ ሥራችን ስኬታማነት ምቹ ሁኔታን በመፍጠር በኩል በተደራጀ አግባብ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል ።
በመጨረሻም የአብክመ ርዕሠ መስተዳድር ክቡር አቶ አረጋ ከበደ ሲያጠቃልሉ ሁሉም ዞን ፕሮጀክቶቹን አንድ በአንድ አውቀው እንዲመሩ እና በዞንም ሆነ በወረዳ ደረጃ መፈታት የሚችሉትን የነዳጅ ፣ጠጠር፣ የአሸዋና መሰል ግብዓቶችን ችግር በመፍታት በኩል እንዲሁም ከህ/ሰብ ጋር በመቀናጀት የሚፈቱ የሦስተኛ ወገን ና የፀጥታ ችግሮችን በመፍታት በኩል ሙሉ ትኩረት እንዲደረግ ገልፀው በተለይ ምዕ/ጎንደር ሠፊ የውሃ ሃብት ፀጋ ባለቤት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአካባቢውን ህ/ሰብንም ሆነ ክልላችንን ተጠቃሚ ለማድረግ ለተጀመሩ ትላልቅ የመስኖ ሥራዎች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በኩል አተኩረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
እንደ ማጠቃለያ አቶ አረጋ ከበደ ሲገልፁ ከትናንሽ እስከ ትላልቅ ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን ሥራም ሆነ የግንባታ ሥራዎች መሠረታዊ ለውጥ (paradigm shift ) ሊያመጣ በሚችል አግባብ በያዝነው ዓመት በትኩረት እንዲፈፀም አቅጣጫ በመስጠት መድረኩ ተጠናቋል።