“ምርታማነትን ለማሳደግ የመስኖ አውታሮችን በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በመረጃ መደገፍ ይገባል” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

“ምርታማነትን ለማሳደግ የመስኖ አውታሮችን በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በመረጃ መደገፍ ይገባል” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

አዲስ አበባ: የካቲት 05/2017 ዓ.ም(አሚኮ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያው “የመስኖ እና የአየር ንብረት ለውጥ ለማይበገር ምርታማነት ጉባኤ 2025” እየተካሄደ ነው።ጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም የተሻለ የኑሮ ዘይቤ እና የመስኖ ልማትን ለማጎልበት ዓለምአቀፋዊ ልምድ እና ተሞክሮዎችን ለመቀመር የሚያስችል ነው ተብሏል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጣ የምግብ ዋስትና ችግርን ለመቅረፍ የአረንጓዴ አሻራ እና የሌማት ትሩፍት መርሐግብሮችን እየተገበረች መኾኗን ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ አልፎ እንደአህጉር ለአየር ንብረት ለውጥ አይበገሬ ምርታማነትን ለመገንባትም የመስኖ አውታሮችን በፍይናንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በዕውቀት፣ በመረጃ መደገፍ እና ማልማት ይገባል ብለዋል።

አፍሪካ ያላትን ሀብት እና አቅም በአግባቡ መጠቀም ከቻለች እራሷን መመገብ እንደምትችልም ተናግረዋል። የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በዘላቂነት መቋቋም የሚችል የግብርና ሥርዓትን ለመገንባት እየሠራች ነው ብለዋል። እንደሀገር የመስኖ አውታሮችን ለማስፋፋት በመንግሥት ከፍተኛ ጥረት በርካታ ሥራዎች ቢሠሩም ዘርፉ ከሚጠይቀው ፋይናንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ዕውቀት አንፃር ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ዓለምአቀፋዊ ጉባኤ ማካሄድ አስፈላጊ መኾኑንም አንስተዋል።

ጉባኤው የመንግሥት እና የግሉን ዘርፍ በፋይናንስ ለማስተሳሰር፣ የሴቶች እና ወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚያስችልም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ እና ለም መሬት በመስኖ በማልማት የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ርብርብ የሚያግዝ ይኾናልም ተብሏል። በዚህ ዓለምአቀፍዊ ጉባኤ ላይ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን፣ ሚኒስትሮችን ጨምሮ ተመራማሪዎች፣ የዘርፉ ደጋፊ አካላት እና የልማት ድርጅቶችም ተሳታፊ ናቸው።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top