በክልሉ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 28 የመስኖ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ማጠናቀቅ ተችሏል – ቢሮው
ባህር ዳር፤ ግንቦት 3/2017፦ በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመገንባት ላይ ከነበሩ የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል 28ቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት መዘጋጀታቸውን የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ዳኝነት ፈንታ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት ክልሉ ያለውን ዕምቅ የውሃ ሃብት በአግባቡ በመጠቀም በበጋ መስኖ ልማት የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
ለዚህም በዘንድሮው በጀት ዓመት የክልሉ መንግስት በመደበው 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የ154 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከእነዚህ መካከል የ95 ፕሮጀክቶችን ግንባታ በተያዘው በጀት ዓመት አጠናቆ በቀጣይ ዓመት የበጋ ወቅት ከ4ሺህ 500 ሄክታር በላይ ተጨማሪ መሬት ወደ ልማት ለማስገባት ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ለዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተደረገው ጥረት የ28 ፕሮጀክቶች ግንባታ ስራ ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቅ መቻሉን አስታውቀዋል።
ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን እየተከናወነ ባለው የልማት ስራ አንዳንድ ፕሮጀክቶች እስከ ሃያ ወራት ሊወስዱ ይችሉ የነበረውን የግንባታ ጊዜ በተቋራጮች ቁርጠኝነትና በቢሮው ድጋፍና ክትትል ከአምስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ማጠናቀቅ መቻሉን ጠቁመዋል።
በግንባታ ላይ የሚገኙ ሁሉም የመስኖ ፕሮጀክቶች በቀጣይ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ በአዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶቹ ብቻ 23ሺህ ሄክታር ተጨማሪ መሬት በማልማት በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ሂደት እንደሚያግዙ አስታውቀዋል።
እንዲሁም ቀደም ሲል ተገንብተው በአጠቃቀምና በአያያዝ ችግር ምክንያት ተበላሽተው አገልግሎት አቋርጠው የቆዩ ከሃያ በላይ ነባር የመስኖ ፕሮጀክቶች ጥገና ስራም እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
እየተከናወኑ በሚገኙ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታና ጥገና ስራ ከ23ሺህ ለሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢዜአ