67 የመስኖ ፕሮጄክቶች እየተገነቡ መኾናቸውን የአማራ ክልል መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አስታውቋል።
ባሕር ዳር: መጋቢት 03/2017 ዓ.ም የአማራ ክልል መንግሥት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የመስኖ ፕሮጀክቶችን የማስፋፋት ሥራ እያከናወነ መኾኑን አስታውቋል። የአማራ ክልል መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየልኝ መሳፍንት አርሶ አደሮች ከዝናብ ጥገኝነት ተላቀው በዘመናዊ መስኖ ልማት ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተሠራ ነው ብለዋል። በተያዘው በጀት ዓመት ከ23 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት የሚያስችሉ 154 የመስኖ ፕሮጀክቶች ለመሥራት መታቀዱን ያነሱት ምክትል ኀላፊው 67 ፕሮጄክቶች ወደ ግንባታ መግባታቸውን ተናግረዋል። 4 ፕሮጀክቶች ደግሞ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል። ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ ከ53 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚኾኑም ይጠበቃል።በተጨማሪም ሌሎች 17 የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ውል ተፈጽሟል ነው ያሉት። 110 ፕሮጀክቶች የጥናትና ዲዛይን ሥራ እየተከናወነላቸው መኾኑም ገልጸዋል። በክልሉ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ሊለማ የሚችል እንደሚችል የተናገሩት ምክትል ኀላፊው እስካሁን ድረስ ጥቅም ላይ የዋለው 10 በመቶ ብቻ ነው። እንደ ኢዜአ ዘገባ የመስኖ ፕሮጀክቶችን የማስፋፋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ይህ ጥረት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል። ዘገባው የአሚኮ ነው


