ዶ/ር-ኢ ዳኝነት ፈንታ ለመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ በማለት የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል!!!
ባህርዳር
ሚያዚያ 2016 ዓ.ም
መገጭ በተስፋ የሚጠበቀው ግድብ”
ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መገጭ ብዙ ተስፋዎች የተጣሉበት ግድብ ነው፡፡ ውኃ ለሚጠማት ጎንደር ከተማ፣ በመስኖ ለማልማት ተስፋ ለሚያደርጉ አርሶ አደሮች በጉጉት ሲጠበቅ ኖሯል፡፡ መገጭ ግን ጉዞው አዝጋሚ ኾነ፡፡ መገጭ ረጅም ዓመታትን ወሰደ፡፡
የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች የመገጭን መጠናቀቅ ዛሬም በጉጉት እየጠበቁ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለዓመታት ሳይጠናቀቅ የቆየውን ግድቡን ለማጠናቀቅ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ እርሳቸው የሰጡት መመሪያ ግድቡን ሊያጠናቅቀው እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የጎንደር ከተማ ነዋሪው አቶ አዱኛ እሸቴ የጎንደር ሕዝብ መገጭ ይጠናቀቃል ብሎ በተስፋ ሲጠብቅ ኖሯል፤ በጠየቅን ቁጥር ሊመረቅ ነው፣ ሥራው እየተፋጠነ ነው፣ እዚህ ደረጃ ደርሷል ይሉናል፤ ግን ያሉንን አናይም፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተስፋ እያጣን ነው የሄድነው ይላሉ፡፡ መገጭ ደርሷል ካሉን በኋላ መልሶ ፈረሰ አሉን፣ ታዲያ ይሄን ምን እንለዋለን? በማለት ይጠይቃሉ፡፡
መገጭ ተስፋ እያጣንበት የመጣ ግድብ ነው ይሉታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መገጭን በተመለከተ የሰጡት መመሪያ መልካም ነው፣ ራሳቸው ከመሩት ለጥቅም ሊያበቁት ይችላሉ፤ ሕዝቡ ተስፋ ብልጭ ካለለት በደስታ ነው የሚያግዘው ብለዋል፡፡
የጎንደር ሕዝብ ልማትን ይደግፋል፡፡ መንግሥት የልማት ሥራዎች ውጤታማ እንዲኾኑ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡ ዘላቂ የኾነ ሰላም እንዲመጣ ማድረግ አለበትም ብለዋል፡፡
የጎንደር ሕዝብ ለሚሠራ ድጋፉን ሳይሰስት ይሰጣል፤ ምንም ወደ ኋላ የሚለው ነገር የለውም፤ የጎንደር ሕዝብ ልማትን በእጅጉ ይፈልጋል፤ ዘላቂ የኾነን የልማት ሥራ ይፈልጋል፤ መንግሥት ይሄን ካደረገልን እጅግ እናመሠግነዋለንም ብለዋል፡፡ ሰላም እና ልማት በጋራ እንዲሄዱ እንፈልጋለን፣ ሰላም ከሌለ ዛሬ የተሠራው ነገ ይፈርሳል ነው ያሉት፡፡
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መመሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት መገጭ ረጅም እድሜ ካስቆጠሩ ፕሮጀክቶች መካከል አንደኛው ነው፡፡ የመጀመሪያው የተቋራጭ ውል የተፈረመው በ2001 ዓ.ም መኾኑን አስታውሰዋል፡፡ ውሉ ሲፈረም 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ተቆርጦለት እንደነበርም አንስተዋል፡፡ ውሉ ከተፈረመ በኋላ ለአራት ዓመታት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሳይደረግ መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ ከአራት ዓመት በኋላ ለአራት ዓመታት የሚቆይ ውል መፈረሙን አመላክተዋል፡፡ የንድፍ ችግር የነበረበት እና በደንብ ተጠንቶ ያልተገባ ስለነበር የግድቡ ሥራ ሳይጀመር መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ የሁለተኛው ውል ስምምነት አዳዲስ ሥራዎችን ለመጨመር እና ሌሎችን ለማየት ለአንድ ዓመት ተጨማሪ ውል ተሰጥቶት መታየቱንም ተናግረዋል፡፡ ዋጋውም ወደ 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱን ነው የገለጹት፡፡ ይሄም ኾኖ የተፈለገው ውጤት ባለመገኘቱ ተጨማሪ ውል እንደተፈረመም አንስተዋል፡፡
ከሦስተኛው ውል በኋላ የተሻለ ሥራ ተሠርቶ እንደነበር ያነሱት ሚኒስትሯ ግድቡ የመንሸራተት አደጋ ገጠመውና ግንባታው እንዲቆም ተደርጎ እንደገና እንዲታይ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ አዲስ ውል እና አዲስ ዋጋ ተቆርጦ ወደ ሥራ መገባቱንም አመላክተዋል፡፡ አሁን ላይ ዋጋው 6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መድረሱንም አመላክተዋል፡፡ በርካታ ተጨማሪ ሥራዎች ገና ይቀሩታል ነው ያሉት፡፡
የአፈር መንሸራተት ከማጋጠሙ አስቀድሞ 78 በመቶ ደርሶ እንደነበር የተናገሩት ሚኒስትሯ አሁን ላይ ከ66 እስከ 68 በመቶ መድረሱንም ተናግረዋል፡፡ የተናደው አፈር ወጥቶ በሚፈለገው ጥራት እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል፡፡ የመፈጸም አቅም፣ የገንዘብ እና የቴክኒክ ችግሮች እንዳሉበትም ተናግረዋል፡፡ በጥንቃቄ ሳይታይ የተገባበት ፕሮጀክት ስለ ነበር ለችግሮቹ መደራረብ መንስኤ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ኀላፊነት ወስደን በጥንቃቄ ለመሥራት ተዘጋጅተናልም ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከለውጥ በፊት የጀመረው የመገጭ ግድብ ባለመጠናቀቁ ምሬት እና ጥያቄ መኖሩንም አንስተዋል፡ ግድቡ እንዴት እንደሚጠናቀቅ ምክክር እና አቅጣጫ ይፈልጋልም ብለዋል፡፡
መገጭ ለውጡ እስኪመጣ ድረስ 10 ዓመት መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በእነዚያ ዓመታት ውስጥ ከአራት እስከ አምስት እንደ መገጭ ዓይነት ግድብ ሊሠራ ይችላል፤ የመጀመሪያው ውል አራት ዓመት ነው አላለቀም፤ በሁለተኛው ውልም አላለቀም፣ ለማሻሻያ አንድ ዓመት ተሰጠው አላለቀም፣ 10 ዓመት ከቆየ በኋላ ዛሬ ላይ ስናዬው ፕሮጀክቱ ተጨማሪ ሃብት ይፈልጋል፤ ተጨማሪ አመራር ይፈልጋል፤ የተለየ አካሄድ ካልተጠቀምን በስተቀር ግድቡን መጨረስ አንችልም ብለዋል፡፡
ለጎንደር ሕዝብ መገጭ የሚባል ግድብ ልንሠራልህ አንችልም ብንለው ይሻል ነበር፤ እንችላለን ብለን ጀምረን 10 ዓመት በተስፋ እና በጉጉት ከምናስቀምጠው ሲጀመር ብቃቱ የለንም ብለን ባንጀምረው ይመረጥ ነበር፤ ገንዘብ ፈሰሰ፣ ጊዜ ባከነ፣ ሕዝብ ተማረረ ሥራው ግን አላለቀም ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ባስቀመጡት አቅጣጫ የመገጭ ግድብን ውል በአጭር ጊዜ እንዲሰረዝ፣ አሁን እየሠራ ያለው ኩባንያ ኮንትራቱን ሰርዞ፣ አቅም ያለው መሥራት የሚችል ኩባንያ ውል ፈርሞ ሚኒስቴሩ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ሪፖርት ለጠቅላይ ሚኒስሩ እንዲያቀርብ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ በሚቋቋም ኮሚቴ ክትትል እንደሚደረግበትም አስገንዝበዋል፡፡ የሚኒስቴሩ የውጤት ማረጋገጫ መገጭ ነው የሚኾነው ነው ያሉት፡፡
ግድቡ የእኛን ጨምሮ 15 ዓመት ዘግይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ግድቡን ገድበን የውኃ ችግር ለመፍታት የሚያስችል ብቃት እንድንፈጥር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የሚያስፈልገውን የገንዘብ ጉዳይ ገንዘብ ሚኒስቴር ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡ ይሄን በማድረግ ለጎንደር ሕዝብ ለመሥራት ፍላጎት እንዳለን ማሳየት አለብን ብለዋል።