የሽንፋ የተቀናጀ ከፍተኛ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት በያዝነው አመት የጥናትና ዲዛይን ስራውን በማጠናቀቅ ለግንባታ ዝግጁ የማድረግ ሥራ እንደሚሰራ ተገለጸ፡፡
ባህርዳር ህዳር 17/2017 ዓ.ም
መድረኩ በባህርዳር ከተማ የፌደራል መስኖና ቆላማ አካባቢ ሚንስቴር ከፍተኛ መሃንዲሶችና ባለሞያዎች የክልል ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ምሁራን በተገኙበት የጥናትና ዲዛይን የአዋጭነት ግምገማ ወርክሾፕ ተካሄዷል፡፡
ግድቡ በፌደራል መስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ባለቤትነት በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገነባ ፕሮጀክት ሲሆን የአማራ ክልል ልህቀት የዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ደግሞ የጥናት፣ የዲዛይን እና የማማከር ሥራውን የሚሰራበት ከ 85 ሺህ ሄክታር በላይ በማልማት በቋራ እና መተማ ወረዳ የሚገኙ የ18 ቀበሌ ነዋሪዎችን በሙሉ ወይም በከፊል ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ግዙፍ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት ነው፡፡
በመድረኩ የሽንፋ መስኖ ግድብ የጥናትና ዲዛይን ሰነዱ በተለያዩ የዘርፉ ሞያተኞች ቀርቦ በባለድርሻ አካላት ውይይት የደረገበት እና ጠቃሚ ሞያዊ ማስተካከያዎች እና ጥናቱን ሊያዳብሩ የሚችሉ ተጨማሪ አስተያየቶች ተካተውበት በቀጣይ ጊዜያት ቀሪ ስራዎች በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ በሚቻልበት መንገድ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
በመድረኩ ማጠቃለያ አቶ አየልኝ መሳፍንት የአብክመ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ም/ሃላፊ እንዳሳሰቡት የሽንፋ መስኖ ግድብ የጥናትና ዲዛይን ስራው ከተጀመረ ረዘም ያለ ዓመትን ያስቆጠረ ቢሆንም በተለያዩ ሀገራዊና ክልል አቀፍ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት መዘግየቱን ያስረዱ ሲሆን ፕሮጀክቱ አርሶአደሩን ከዝናብ ጠባቂነት በማላቀቅ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ በኩል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ያስረዱ ሲሆን ለፕሮጀክቱ እውን መሆን የመንግስት እና ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲሁም የአካባቢውን ማህበረሰብ ተሳትፎና ባለቤትነት በማረጋገጥ በኩል ትኩረት አድረገን መስራት ከቻልን ከጸጥታ ጋር ተያያዥ ችግሮችን መሻገር እንደምንችል አሳስበዋል፡፡
ዶ/ር ዘለቀ አንሉ የር/መስተዳድሩ ልዩ አማካሪ እንደተናገሩት ለሽንፋ ፕሮጀክት እውን መሆን የኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ሁላችንም በደንብ መረዳት ከቻልን ሌት ተቀን ሊያስጨንቀን እንደሚገባ እና ትርጉም ባለው መልኩ የምግብ ሉአላዊነትን በማረጋገጥ በኩል አስተዋጽኦው የጎላ ፕሮጀክት መሆኑን በማስረዳት በቀጣይ በወረቀት ላይ ተንጠልጥሎ የቆየውን ጊዜ ሳይወስድ መሬት በማስነካት በኩል የልህቀት ኮርፖሬሽኑም ሆነ ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታችንን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባ በመጠቆም የክልሉ መንግስትም ለፕሮጀክቱ እውን መሆን የትኛውንም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡
በመጨረሻም ኢ/ር ያሬድ ሙላት የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚንስቴር የመስኖ ፕሮጀክቶች ተ/መሪ ስራ አስፈጻሚ በበኩላቸው ሚንስቴር መ/ቤቱ የሽንፋ ፕሮጀክት ካለው ሀገራዊ ኢኮኖሚ ጠቀሜታ እና ከፕሮጀክቱ አዋጭነት አንጻር በተለየ ትኩረት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን በመግለጽ በያዝነው አመት የጥናትና ዲዛይን ስራው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለግንባታ ስራ ዝግጁ መሆን እንዳለበት በመግለጽ የአመካሪ ድርጅቱም ሆነ የክልሉ መንግስት ተገቢውን ክትትል እና ድጋፍ እንዲያደረግ ጥሪ በማስተላለፍ መድረኩ ተጠናቋል፡፡