የአማራ ክልል የገጠር ዘርፍ ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ላይ ተወያይተዋል። በውይይቱ የክልሉ መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮም ሪፖርቱን አቅርቧል።
የቢሮው ኀላፊ ኢንጅነር ዳኝነት ፈንታ (ዶ.ር) የቢሯቸው ተልዕኮዎች ዘመናዊ የመስኖ ግንባታዎች ሥራ፣ የመስኖ አውታሮች ጥገና፣ አማራጭ የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብ እና የአሥተዳደር ሥርዓት መገንባት መኾኑን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ በጥናት እና ዲዛይን 79 ሺህ ሄክታር ማልማት የሚችሉ 53 ነባር ፕሮጀክቶችን፤ በአዲስ ደግሞ 2 ሺህ 900 ሄክታር ማልማት የሚችሉ 53 ፕሮጀክቶች በድምሩ 110 ፕሮጀክቶች የጥናት እና ዲዛይን ሥራ ይሠራላቸዋል ብለዋል። በዚህ በጀት ዓመትም የ82 መስኖ ፕሮጀክቶች ጥናት እና ዲዛይን ሥራ ተጠናቅቆ ለሚቀጥለው በጀት ዓመት ግንባታ ሥራ ይደርሳሉ ብለዋል።
በግንባታ በኩል በተለያዩ ፕሮግራሞች 23 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የሚችሉ 156 ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ዶክተር ዳኝነት 95ቱን በበጀት ዓመቱ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ብለዋል። በመስኖ ዙሪያ የሚሠሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ አጋር አካላት እና የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ፕሮጀክቶችም መኖራቸውን አስታውሰዋል።
ከዚህ በፊት ተገንብተው ያልተጠናቀቁ እና የተበላሹ 23 የመስኖ ፕሮጀክቶችን ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባትም እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በቢሮው የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ በኩልም 980 የውኃ መሳቢያ ሞተሮች ግዢ ተፈጽሞ እየተሰራጨ ነው ብለዋል። የተገነቡ የመስኖ ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጡ ማኅበረሰቡ ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያደርግላቸው እና የመስኖ አጠቃቀማቸውን እንዲያዘምኑ 230 የመስኖ ተጠቃሚ ማኅበራትን የማጠናከር ሥራ እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ለሥራው ከተለያዩ የበጀት ምንጮች 2 ቢሊየን ብር በጀት መመደቡንም ገልጸዋል። በግንባታዎችም ለ25 ሺህ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት።
ከዩንቨርሲቲ ተመርቀው የተደራጁ ወጣቶች አነስተኛ የመስኖ ግንባታዎችን እንዲሠሩ እየተደረገ ነው። የውኃ መሳቢያ ሞተሮችንም ለወጣቶች በመስጠት በመስኖ ልማትም እንዲሳተፉ መደረጉን ጠቅሰዋል። በትላልቅ የግንባታ ሥራዎችም ወጣቶች የበለጠ ተጠቃሚ እንደኾኑ ነው የገለጹት።
የመቋረጥ እና የመዘግየት ችግር ያጋጥማቸው የነበሩ በኢንተርፕራይዞች የሚገነቡት የመስኖ ፕሮጀክቶችን
አሠሪ ተቋሙ ኀላፊነቱን ወስዶ በጀቱን ከኢንተርፕራይዞቹ ጋር በጋራ በማሥተዳደር ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በፌዴራል መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር እስከ 200 ሺህ ሄክታር የሚያለሙ አምስት የመስኖ ሜጋ ፕሮጀክቶች የጥናት እና ዲዛይን ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
መገጭ፣ ላይኛው ርብ፣ ታችኛው ርብ፣ አጅማ ጫጫ እና ጣና በለስ መስኖ ፕሮጀክቶችም ግንባታቸው እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል። አብዛኞቹም ረጂም ጊዜ ስላስቆጠሩ ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ ከክልሉ መንግሥት እና ከመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ለማስተካከል ጥረት አድርገናል ብለዋል። የዘገየውን የመገጭ ግንባታ ተቋራጭ በሌላ የመተካትን እርምጃም በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የሌሎቹንም ግንባታዎች እየተከታተልን እና እየተወያየን ለማጠናቀቅ ጥረት እያደረግን ነው ያሉት ኀላፊው የጸጥታው ችግር ግብዓት ለማቅረብም ኾነ ለመከታተል ማስቸገሩን ተናግረዋል።
ቆቦ ጊራና በሀገር ደረጃ ትልቅ አቅም ያለው የመስኖ ፕሮጀክት መኾኑን እና 65 የሚኾኑት ጥልቅ የመስኖ ጉድጓዶች ሥራ ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል። በነበረው ጦርነት የደረሰበትን ከፍተኛ ጉዳት ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባት በክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት ትብብር እየተሠራ ነው ብለዋል።
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር 31 ጠላቂ ፓምፖችን ድጋፍ ማድረጉን እና በክልሉ ቢሮ ደግሞ የ26 ትራንስፎርመር ግዢ መፈጸሙን ገልጸዋል። በዚህም ቆመው የነበሩ 30 ጉድጓዶች ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል። የበለጠ ለማስፋፋትም የኤሌክትሪክ ኃይል እና ለጥናትና ዲዛይን የበጀት እጥረትን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሣህሉ (ዶ.ር) መስና እና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ ከተቋቋመ ሦስት ዓመቱ መኾኑን ጠቁመዋል። ቆላማ አካባቢዎች በተለምዶ ሰሊጥ እና አኩሪ አተር በመኽር ከማምረት ያለፈ ገና ሥራ አልተጀመረም። አካባቢዎቹ ያላቸውን የውኃ እና ሌሎች ሃብቶች በመጠቀም በዓመት ሦስት ጊዜ የማምረት ሂደት መጠናከር አለበት ብለዋል።
ክልሉ የገጠመው የሰላም ችግር በሙሉ አቅማችን እንዳንሠራ አድርጎናል፤ በቀጣይ የሰላሙን ሁኔታ ትኩረት ሰጥተን በመሥራት ልማቱንም አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።
አሚኮ